የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ እየተሰራ ነው

ሚያዚያ 10/2016(ኢ.ማ) የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው::

የ2016 ኢትዮጵያ ታምርት 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በመጪው ሚያዝያ 13 በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ ኢትዮጵያ ታምርት የሩጫ ውድድር ከ22 ክለቦች የተውጣጡ አትሌቶች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የእድገትና ተወዳዳሪነት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ሩጫውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ የሩጫ ውድድሩ የሚካሄደው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ነው ብለዋል።

በተለይም በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ የስፖርት ትጥቆችን ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና በዘርፉ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያለመ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ውድድሩ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከስፖርቱ ጋር በማስተሳሰር አምራቹ የሰው ኃይል ጤንነቱ ተጠብቆ የማምረት አቅሙን ለማጎልበት ታስቦ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ለማስተዋወቅና የመጠቀም ባህልን ለማሳደግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ ምርቶችን በሰፊው በማምረትና የመጠቀም ባህልን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በእጅጉ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሥር ዓመት የልማት መሪ ዕቅድ ስትራቴጂክ የሆኑ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶችን በማስፋፋት የሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶችን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

Share this Post