ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ማምረት የሚያስችል ግብዓት ያላት በመሆኑ በዘርፉ መሰማራት አዋጭ ነው (አቶ ዱጋሳ ዱንፋ)
መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (ኢሚ) በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዕድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ አማካሪው የቻይና ሻንጋይ ላውንች አውቶሞቲቭ ጉባንያ ኃላፊዎችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ ።
በውይይታቸው ወቅት የዕድገትና ተወዳዳሪነነት ዘርፍ አማካሪው አቶ ዱጋሳ ዱንፋ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የተስማማ አምራች ኢንዱስትሪን መገንባት ተቀዳሚ ዓለማዋ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከማስገባት ባለፈ በሀገር ውስጥ በማምረት ለተጠቃሚው ማቅረብና ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላካ በትኩረት እየሰራች ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ጥቂት አምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያዎች በስራ ላይ መሆናቸውን የገለፁት አማካሪው መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ ከ4 በላይ የሚሆኑ የውጪ ሀገር ካምፓኒዎች በዘርፉ ለመሰማራት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የባትሪ ምርት ጥሬ ዕቃ ማዕድን ያላት ሀገር በመሆኗ የቢዋይዲ( BYD )የኤሌክትሪክ መኪና ዲዛይን ባለቤት የሆነው ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ቢጀምር ትርፋማ እንደሚሆን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ለተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች የምትሰጠውን ድጋፍና ማበረታቻ የተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
የሻንጋይ ላውንች አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጅ ኩባንያ ዋና ማናጀር ሚስተር ው ሻኦሁና (Mr. Wu Shaohuna) በበኩላቸው ኩባንያቸው በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የዲዛይን አገልግሎትን ጨምሮ የምርምርና ልማት ማዕከልን በማቋቋም ኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልጉ ገልፀው በተጨማሪም knocked-down (KD) የተሽከርካሪ ክፍሎችን በማምረት እና ወደ አገራችን የመኪና ክፍል መገጣጠሚያ ላቋቋሙ ፋብሪካዎች በመላክ በዘርፉ ለተሰማሩ የኢትዮጵያ የግል ኩባንያዎች ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ በአነስተኛ ዋጋ ከፍተኛ የማምረት አቅም እንዲኖራቸው በማስቻል በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ።
ማናጀሩ አክለውም ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የኤሌክትሪክ መኪና ብራንድ እንዲኖራት መስራት ፍላጎታቸው መሆኑን በመጥቀስ በዘርፉ ተሰማርተው የሚሰሩ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን እየጎበኙና ውይይትም እያከናወኑ እንደሆነ ገልፀዋል።
የቢዋይድ (BYD) ኤሌክትሪክ መኪና ዲዛይን ባለቤቱ ሻንጋይ ላውንች አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጅ ኩባንያ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴና የዕድገት ደረጃን የተመለከተ ማብራሪያም አቅርበዋል::
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት