በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወነ ሥራ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ። (አቶ መላኩ አለበል)
መስከረም 13/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢትዮጵያ መድሃኒትና ሕክምና መገልገያዎች አምራቾች ዘርፍ ማህበር 22ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በኢትዮጵያ መድሃኒት እና ሕክምና መገልገያዎች አምራች ዘርፍ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠሩን ገልፀዋል።
በተለይም ባለፋት ሶስት ዓመታት የአምራች ዘርፋ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በመንግስት በኩል የተደረጉ የአሰራር ስርዓት ማሻሻያዎች ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለአብነትም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወነ ሥራ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በዚህም ለጤና ዘርፍ ከውጭ የሚገቡ የመድኃኒትና ህክምና መገልገያ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።
በአምራች ዘርፋ የተጀመረውን መነቃቃት ለማጠናከርም የፋይናንስ አቅርቦትን ከማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ አሠራርን ከማቀላጠፍ፣ የመሰረተ ልማት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር እና የገበያ ትስስርን ከማስፋት ጋር በብሔራዊ አምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል ።