አምራች ኢንዱስትሪዎች የኤክስፖርት አፈፃፀም አቅማቸውን ለማሳደግ በድርጅታቸው ውስጥ ያለውን የአስተዳደር ችግር መፍታት አለባቸው ። ( አቶ መላኩ አለበል)

መስከረም 7/2018 ዓ.ም (ኢ.ሚ) አምራች ኢንዱስትሪዎች መንግስት ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ባሻገር የኤክስፖርት አቅማቸውን ለማሳደግ በድርጅታቸው ውስጥ ያለውን አስተዳደራዊ ችግር ራሳቸው መፍታት እንዳለባቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል ገለፁ ፡፡

አቶ መላኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኤክስፖርት አቅማቸውን ለማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ በሚችሉ አሰራሮች፣ የባለሙያዎችን ክህሎት ከማሳደግና ከምርት ጥራት አኳያ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

በኤክስፖርት አፈፃፀማቸው ዝቅ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከተሻሉት ተሞክሮ መቅሰምና ጥሩ አፈፃፀም እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ማነቆዎቻቸውንም መፍታት አለባቸው ያሉት ሚንስትሩ ለወደፊት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኤክስፖርት አቅም ለማነቃቃት ሁሉንም የኤክስፖርት ምርቶች ያካተተ አካታች የማበረታቻ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ጥሩ የኤክስፖርት አፈፃፀም ያሳዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅማቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ከዕቅዳቸው አንፃር ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ደግሞ ተቋማቸውን ፈትሸው አዲስ የአሰራር ስልት መቀየስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

Share this Post