ቻይና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እድገት የምታበረክተው አስተዋፅኦ ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ለጀመርነው ስራ አጋዥ ነው (አቶ መላኩ አለበል)

መስከረም 15/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የቻይና የኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሊ ሊቸንግ የተመራ ልዑክ ጋር በኢትዮጵያና ቻይና መንግስት መካከል ጠንካራ የጋራ መግባባትን ለማጠናከርና ታላላቅ ተግባራትን በጋራ ለማከናወን እና መሠረት ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

አቶ መላኩ አለበል በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች ያሉት ሚኒስትሩ በኢንዱስትሪ ልማት ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሥነ ምህዳር በመፍጠር ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗንም ገልፀዋል ።

ቻይና የኢትዮጵያ አጋር በመሆን ለዓመታት መቆየቷን የገለፁት አቶ መላኩ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንቨስትመንት የተመቸ ሥነ ምህዳር ፈጥራለች ብለዋል።

ቻይና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በታዳሽ ሀይል ልማት፣ በመንገድና ባቡር መሰረተ ልማት በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እድገት የምታበረክተው አስተዋፅኦ ኢትዮጵያን የቀጣናው የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ለጀመርነው ስራ አጋዥ ነው ያሉት አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የኢንዱስትሪ ልማትን ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በተሰጠ ልዩ ትኩረት ተኪ ምርትን ማሳደግ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ምርት በመጠን፣ በአይነትና ጥራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻልና የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ መቻሏን የጠቀሱት አቶ መላኩ ኢትዮጵያን ተገማችና ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

የቻይና ባለሀብቶች ተሳትፎ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የክህሎት ልማት፣ ኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ኢንዱስትሪን ዕውን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት የቻይና ባለሀብቶች ሚና የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን መደገፍ የሚያስችል የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ መዘርጋቷን ጠቅሰው፤ ቻይና ብቁ የኢንዱስትሪ አስተዳደር አቅም እንድንገነባ እገዛ አድርጋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት ሰፊ ገበያ፣ የተሟላ መሰረተ ልማት፣ ቴክኖሎጂና ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳላት ጠቅሰው፣ ቻይናን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይና የኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሊ ሊቸንግ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የቻይና ወሳኝ አጋር መሆኗን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ቻይና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰው፣ ለኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ቅድሚያ ትሰጣለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና ቻይና ትብብር እያደገ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እሴት በሚጨምሩ የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች ላይ በስፋት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማነቃቃት ወሳኝ እርምጃ በመውሰዷ ለውጭ ኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኗን ተናግረዋል።

Share this Post