የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አዲስ እመርታን ያመጣል(አቶ ታረቀኝ ቡልልታ)
መስከረም16/2018 ዓ.ም(ኢ.ሚ)በኢትዮ-ቻይና አብሮ የመስራት የስምምነት መርሀ ግብር ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ እድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ እንደገለጹት የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አዲስ እምርታን የሚያመጣ ብለዎል።
አቶ ታረቀኝ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ቀደም ሲል በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ የነበረውን የሀይል መቆራረጥ ችግር ሙሉ በሙሉ የፈታ መሆኑን በመጥቀስ መንግስት በዘርፈ ለሚሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ምቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባት ባሻገር አስቻይ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎች ስለተቀረጸ አሁን ላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ብዝኃነት ያለው የኤክስፖርት ምርት ለማምረትና ገቢ ምርቶችን በብቃት የመተካት ስራቸውን እንዲሰሩ የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አብሮ በቅንጅት ለመስራት የሚደረገው ስምምነት ቻይና የብሪክስ ሀገራት መስራች እንደ መሆኗ መጠን በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል የሚፈለገውን በትብብር ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚያመጣ አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በሁለቱም ሀገራት መካከል አብሮ ለመስራት እንዲቻል የተዘጋጀው የውይይት መርሀ ግብር ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለማሳየት ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው ሰምምነቱ የኢትዮጵያን የኤክስፖርት አቅም እንደ ሚያሳድግና በአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ የተደገፉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠርና ለማስፋፋትም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ የቻይና ልኡካን ማዕድን የሚያመርቱ ግዙፍ የቻይና አምራች ኢንዱስትሪዎች በአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ የሚሰሩበትን ሁኔታ በቪዲዮ(በተንቀሳቃሽ ምስል) ለተሳታፊዎች ያስጎበኙ ሲሆን የኢትዮጵያና የቻይና አምራች ኢንዱስትሪዎች በጋራ አብሮ መስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡