የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሸጋገር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ነው /አቶ መላኩ አለበል/

መጋቢት 29/07/2015 ዓ.ም (አ9ሚ) በኢንዱትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የሚመራው የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ውይይት ተካሄዷል:: ኮሚቴው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉበትን ደረጃ በተመለከተ ፣እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡

የተቀናጀ የግብርና ኢንዱትሪ ፓርኮች በዋናነት የግብርናውን ዘርፍ በማሸጋጋር ረገድ ትልቅ ሚና አለው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እስካሁን ከ140ሺ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ማምረት ከጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ጋር የገበያ ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ይህም በምርት ጥራት እና መጠን እድገት ላይ ቀላል የማይባል መሻሻል መምጣቱን እና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድም ትልቅ ሚና እንዳለው አክለዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም ፓርኮቹን በተሟላ ቁመና ለባለሃብቶች ምቹ ለማድረግ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ፓርኮቹን ከማስተዋወቅ እና የገጽታ ግንባታ ስራዎች በመስራት ረገድ በየደረጃው የተቋቋሙ ኮሚቴዎች በተያዘላቸው የግንኙነት አግባብ ስራዎችን ገምግሞ አቅጣጫ ከማስቀመጥ ጋር በተያያዘ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ግርማ አመንቴ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ፣ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የገንዘብ ሚኒስቴር ሚ/ዴኤታ፣ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚ/ዴኤታ፣ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱትሪ ፓርክ ሃላፊዎች እና አጋር አካላት በውይይቱ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Share this Post